Admin1
Wed, 09/23/2026 - 11:08
የደንና አካባቢ ጥበቃ ተግባራት በሥራ ዕድልና በጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ድርሻቸው አበረታች መሆኑ ተገለጸ
ዱራሜ፣ መስከረም ፣ 2019 ዓ.ም.
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ የዞኖችና ልዩ ወረዳዎችን የ2018 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም እና የ2019 ዓ.ም. መሪ ዕቅድ ገምግሟል። በግምገማው የተመዘገቡ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች ተዳሰው፤ በ2019 ዓ.ም. ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራትም ተለይተዋል።
የ2019 ዓ.ም. መሪ ዕቅድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ኃላፊዎች የግብዓት እጥረትን ለመቅረፍ በየዘርፉ በሚደረጉ የንቅናቄ መድረኮች የተለያዩ አካላትን በስፋት ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በየአካባቢው የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመርና በማስፋፋት የዘርፉን ሥራ በተሻለ አግባብ መምራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኃላፊዎቹ በ2018 ዓ.ም. ዘርፉ በሕብረተሰብ ተሳትፎና በተግባቦት የታጀበ አካሄድ መመራቱን ጠቁመው፣ ይህንን አሳታፊ አካሄድ በ2019 ዓ.ም. የበለጠ በማጠናከር የሥራውን ውጤታማነት ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል። የደንና አካባቢ ዘርፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመከላከልና በመቀነስ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሥራዎቹን በተቀናጀ አግባብ ማስፈጸምና ከአጋር አካላት ጋር ትብብሩን ማጠናከር እንደሚገባም ተመላክቷል።
በደን ልማት ዘርፍ የሞዴል ችግኝ ጣቢያዎችን በማጠናከርና ተሞክሮዎቻቸውን በማስፋፋት የደን ልማት ሥራዎችን በዘላቂነት ለማስፈጸም ግልጽና የተቀናጀ ስትራቴጂ መከተል እንደሚገባ ተመላክቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ፣ የደንና አካባቢ ዘርፉ ለክልላዊ ኢኮኖሚና ለሀገራዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) የሚያበረክተው ሚና ጎላ ያለ መሆኑን ገልጸዉ ከደን ሀብት የሚገኘውን የሮያሊቲ ገቢ በደንቡ መሠረት በአግባቡ መሰብሰብና ለሚመለከተው የአካባቢ አስዳደር መዋቅር የገቢ ተቋም ገቢ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ።
የሮያሊቲ ገቢ አሰባሰብና የድርሻ አጠቃቀም በደንብና በሥርዓት መመራቱ የዘርፉን የገቢ አቅምና ለክልሉ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ እንደሚያጠናክርም አቶ አብርሃም አመልክተዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የደን ጥበቃና ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ ወልደማርያም፣ በክልሉ የደን ሽፋንን መጠበቅ፣ ማልማትና ማስፋፋት ቀዳሚ ትኩረት የሚሻ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የደን ሀብትን በአግባቡ ለመለየትና ለማስተዳደር የመሬት ካርታ አሠራርን ከጂኦ-ሬፈረንስ መረጃ ጋር በማጣመር ትክክለኛ የመረጃ ሥርዓት መገንባት እንደሚገባም አቶ አድማስ አስረድተዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሎላሞ ሡላሞ፣ በክልሉ የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትን ማረጋገጥና የሕግ አፈጻጸምን ማጠናከር የዘርፉ ትኩረት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
አቶ ሎላሞ በተለይም መርዛማ ኬሚካሎችን በአግባቡ መያዝ፣ መጠቀምና ማስወገድ ለሰው ጤናና ለአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ በመሆኑ፣ በኬሚካሎች አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ ቁጥጥርና ክትትልን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የሴክተር ጉባዔው መድረክ አስተማሪ በሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ዜማዎች፣ ግጥሞችና አጫጭር ድራማዎች ተደምቆ ተካሂዷል። በዜማዎቹ የደን ጥበቃን፣ የአካባቢ ንጽህናንና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን የሚያስተምሩ መልዕክቶች ቀርበዋል፤ ግጥሞቹም የሰውና የተፈጥሮ ትስስርን በማጉላት የጋራ ኃላፊነትን አስታውሰዋል።
በጉባዔው የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ አመራርና ማኔጅመንት አባላት፣ የተለያዩ ባለድርሻ ሴክተሮችና የክልሉ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ደንና አካባቢ ጥበቃ ሴክተር ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።