Admin1
Mon, 09/21/2026 - 11:25
ኢ-ተገማች የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ተግቶ መስራት ይገባል ተባለ
( ዱራሜ ፣ መስከረም 8/2019 ዓ.ም) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ የ2019 ዓ.ም ዓመታዊ የሴክተር ጉባዔ በዱራሜ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምክትል ርዕሰ መስተዳድር የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ ኢ-ተገማች የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም መንግስትና ህብረተሰቡ በቅንጅት ተግተው መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የሀገሪቱ መንግስት ምልዓተ ህዝቡን በማሳተፍ የአረንጓዴ አሻራ ሥራን በማጠናከር ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኡስማን፣ ይህም የአካባቢ ጥበቃንና የአየር ንብረት ለውጥ መላመድን ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ጤናማ አካባቢ ለጤናማ ማህበረሰብና ለዘላቂ ኢኮኖሚ ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን በዘላቂነት በማከናወን ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
አቶ ኡስማን አክለውም፣ ምርታማነት የሚለካው በቁሳዊ ምርት ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ጤናና ደህንነት በማረጋገጥም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችም የረጅም ጊዜ ድምር ውጤታቸው ለሀገር የሚኖረውን ጠቀሜታ በማሰብ መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ደን መትከልና ማልማት ማህበራዊና ስነ-ምህዳራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ፣ በቀጣይም የተጀመሩ የደን ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉና ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው፣ ዓለምና ሀገራችን በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ በዚህም ሳቢያ የአፈር፣ የውሃና የድምፅ ብክለትን ጨምሮ የተለያዩ የአካባቢ ችግሮች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በየጊዜው እያጋጠሙ ላሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ራስን በራስ የመርዳትና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማጠናከር የተያዘውን ዕቅድ በተግባር ለማዋል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውንም አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።
በክልሉ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አቶ አብርሃም በተጨማሪም የተመናመኑ ደኖችን በማገገምና በመጠበቅ በአካባቢና በብዝኃ ሕይወት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።
በጉባዔው የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልሉ ደንና አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ አመራርና ማኔጅመንት አባላት፣ የተለያዩ ባለድርሻ ሴክተሮችና የክልሉ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የልዩ ወረዳ ደንና አካባቢ ጥበቃ ሴክተር ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።