Skip to main content
05
ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር አካባቢን ከቆሻሻ እና ከብክለት ነጻ ማድረግ ይገባል:-
(ዱራሜ ፣ነሐሴ 11/2018) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል "ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ"በሚል መሪ ሀሳብ 3ኛ ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር አካባቢን ከቆሻሻ እና ከብክለት ነጻ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የሀይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ምሁራን፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው አካላት ለዜጎች ምቹ የሆነች ሀገር በመገንባት ሂደት የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉም አቶ ኡስማን ጠቁመዋል።
ያገለገሉ የፕላስቲክ ውጤቶች፣ልዩ ልዩ ኬሚካሎች እና ከፍተኛ ድምጽ የአካባቢ ብክለት በማስከተል ረገድ የጎላ ተጽዕኖ እንዳላቸውም ኃላፊው አብራርተዋል።
የድምጽ ብክለትን ለመከላከል የጋራ ተግባቦት መፍጠር ለችግሩ እልባት መስጠት ያስችላል ሲሉም አቶ ኡስማን ተናግረዋል።
የጽዱ ኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ አጀንዳችን ነው ያሉት ኃላፊው ለዚህም የሁሉንም ህብረተሰብ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
የአካባቢ ብክለት የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በባለቤትነት ሚናውን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ኢተገማች የአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ያለመ ነው ብለዋል።ይህም ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላትን ተቀባይነት የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል።
አካባቢን ከቆሻሻ እና ከብክለት ለመጠበቅ የእይታ ለውጥ ማምጣት ተገቢ ነው ያሉት ኃላፊው ለሰው ልጆች ጤና መጎልበት ልዩ ትኩረት ያሻል ብለዋል።
ጽዱ አካባቢን የመፍጠር ጉዳይ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ የገለጹት አቶ ኡስማን ጉዳዩ በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ለጽዱ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ቀጣይነት ያለው ንቅናቄ በመፍጠር ዘለቄታዊ መፍትሄ መፍጠር እንደሚገባም ኃላፊው አሳስበዋል።
በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት እና ለህብረተሰቡ የመረጃ ተደረረሽነትን ለማረጋገጥ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት እንደሚገባም አቶ ኡስማን በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብረሐም መጫ በበኩላቸው የአካባቢ ብክለት ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ከተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ከስልጣኔ ጋር ተያያዥ ነው ያሉት አቶ አብርሐም በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በአመለካከት ላይ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የጽዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ ንቅናቄ ከግብ ለማድረስ የሁሉንም አካላት የላቀ ድጋፍና ትብብር እንደሚያሻ ኃላፊው አመላክተዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ ህግ ማስከበር ተግዳሮቱ ብዙ ነው ያሉት ኃላፊው ትውልድ የማስቀጠል ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።