Admin1
Mon, 07/27/2026 - 15:21
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን አካባቢ ጥበቃ እና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በዳምቦያ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤት የግንባታ ሥራ አስጀመሩ ፦
(ዱራሜ፣ ሐምሌ 15/2018ዓ.ም) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደን ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ልማት ቢሮ የ2018 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር የአቅመ ደካሞችን ቤት ግንባታ ተግባር የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ በተገኙበት በዳምቦያ ከተማ በይፋ አስጀምሯል።
የቤት ግንባታ ሥራውን በይፋ ያስጀመሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም መጫ እንደተናገሩት፤ ቢሮው ከተሰጠው መደበኛ የልማት ኃላፊነት ጎን ለጎን የመንግሥትና የፓርቲው ዋና ትኩረት የሆነውን ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አጠናክሮ እያከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ኃላፊው አክለውም ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሰው ተኮር ተግባራት በማህበረሰቡ ውስጥ የበጎነት ባህል እንዲዳብር ማድረጋቸውን ጠቁመው፣ እየጠፉ የነበሩ መልካም የማህበረሰብ እሴቶች እንደገና እንዲያንሰራሩና የማህበረሰቡን ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በስፍራው ተገኝተው የተመለከቱትን ሁኔታ አስመልከተው ሲናገሩም "ያየሁት ነገር ቁጭት፣ ደስታና ተስፋን ጭሮብኛል። እስከዛሬ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ገልጠን ማየት ባለመቻላችን ቁጭት፤ ዛሬ የዚህ መልካም ተግባር አካል በመሆኔ ደስታ፤ ወደፊት ደግሞ እነዚህ የበጎ አድራጎት ሥራዎች እያደጉና እየሰፉ ሲመጡ ለሚፈጠረው የተሻለ ነገ ተስፋ ተሰምቶኛል" ብለዋል።
ይህ የሚገነባው ቤት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚከናወን ሲሆን፣ ሀብቱም ከቢሮው ሠራተኞች፣ ከአመራሮችና ጥሪ ከተደረገላቸው በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።
የደምቦያ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ኤርጊቾ በበኩላቸው፤ በጎነት መንፈሳዊ እርካታን የሚሰጥ የማህበረሰብ እሴትና የመንግሥት ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል። ከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመጠገን ባሻገር በማህበረሰቡ ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ በከተማው ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ያደረገውን አርአያነት ያለው ድጋፍ በከተማ አስተዳደሩ ስም ያመሰገኑት ከንቲባው፣ ሥራው በአጭር ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ቤተሰቡ ወደ መኖሪያቸው እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የቤት እድሳት እድል ያገኙት በደምቦያ ከተማ የጌዮጣ ገርባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቄ በሰጡት አስተያየት፤ አሮጌው ቤታቸው ፈርሶባቸው ከልጆቻቸው ጋር በትልቅ ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው ዛሬ አዲስ ቤት ሊገነባላቸው በመሆኑ የተሰማቸውን ላቅ ያለ ደስታና ምስጋና ገልጸዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የደምቦያ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።